ኢያሱ 1:1-7 NASV

1 የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከሞተ በኋላ፣ እግዚአብሔር የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ አለው፤

2 “እነሆ፤ ባሪያዬ ሙሴ ሞቶአል፤ እንግዲህ አሁንም አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሡ፤ ለእሥራኤላውያን ወደምሰጣቸው ምድር ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ።

3 ለሙሴ በሰጠሁትም ተስፋ መሠረት፣ እግራችሁ የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ እሰጣችኋለሁ።

4 የርስታችሁ ዳርቻ ከምድረ በዳው እስከ ሊባኖስ፣ ከታላቁ ወንዝ ከኤፍራጥስ አንሥቶ፣ የኬጢያውያንን ምድር በሙሉ ይዞ፣ በምዕራብ በኩል እስከ ታላቁ ባሕር ይደርሳል።

5 በሕይወት በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ ሁሉ ከአንተም ጋር እሆናለሁ፤ ከቶ አልጥልህም፤ አልተውህም።

6 “ጽና፤ ለቀደሙት አባቶቻቸው እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር እንዲወርሱ፣ ይህን ሕዝብ የምትመራው አንተ ነህና በርታ።

7 አይዞህ፤ ብቻ አንተ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ የሰጠህን ትእዛዝ ሁሉ በጥንቃቄ ጠብቅ፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲሳካልህ፣ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል።