ኢያሱ 10:21-27 NASV

21 ከዚያም ሰራዊቱ ሁሉ በደኅና ተመልሶ፣ ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ መቄዳ መጣ፤ በእስራኤላውያንም ላይ አንዲት ቃል የተናገረ ሰው አልነበረም።

22 ኢያሱም፤ “ዋሻውን ከፍታችሁ እነዚያን አምስቱን ነገሥታት አውጥታችሁ አምጡልኝ” አላቸው።

23 እነርሱም አምስቱን ነገሥታት ማለትም የኢየሩሳሌምን ንጉሥ፣ የኬብሮንን ንጉሥ፣ የያርሙትን ንጉሥ፣ የለኪሶን ንጉሥ የዔግሎንን ንጉሥ አውጥተው አመጡለት።

24 እነዚህን ነገሥታት ባመጡለትም ጊዜ፣ ኢያሱ መላውን የእስራኤልን ወንዶች ከጠራ በኋላ አብረውት የመጡትን የጦር አዛዦች፣ “ወደዚህ ቅረቡና እግሮቻችሁን በእነዚህ ነገሥታት አንገት ላይ አድርጉ” አላቸው፤ እነርሱም ወደ ፊት ቀርበው እግራቸውን በነገሥታቱ አንገት ላይ አሳረፉ።

25 ኢያሱም፣ “አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ በርቱ፤ ጽኑ፤ እንግዲህ በምትወጓቸው ጠላቶች ሁሉ ላይ እግዚአብሔር እንደዚሁ ያደርጋልና” አላቸው።

26 ከዚያም ኢያሱ ነገሥታቱን መትቶ ገደላቸው፤ በአምስትም ዛፎች ላይ ሰቀላቸው፤ ሬሳቸውም እስኪመሽ ድረስ አልወረደም ነበር።

27 ፀሓይ ለመጥለቅ በማዘቅዘቅ ላይ ሳለች ኢያሱ ትእዛዝ ሰጠ፤ ከዚያም የነገሥታቱን ሬሳ ከዛፎቹ ላይ አውርደው ቀድሞ ተደብቀው ወደነበሩበት ዋሻ ውስጥ ጣሏቸው። በዋሻውም አፍ ትልልቅ ድንጋዮች አኖሩ፤ ድንጋዮቹም እስከ ዛሬ ድረስ በዚያ ይገኛሉ።