1 ለይሁዳ ነገድ በየጐሣቸው በዕጣ የተመደበው ድርሻ እስከ ኤዶም ምድር የሚወርድ ሲሆን፣ በስተ ደቡብ መጨረሻ እስከ ጺን ምድረ በዳ ድረስ ይዘልቃል።
2 የደቡብ ወሰናቸው፣ ከጨው ባሕር ደቡባዊ ጫፍ ካለው የባሕር ወሽመጥ ይነሣል፤
3 ከዚያም የአቅረቢምን መተላለፊያ በማቋረጥ በጺን በኩል እስከ ቃዴስ በርኔ ደቡባዊ ክፍል ይደርሳል፤ ደግሞም ሐጽሮንን አልፎ ወደ አዳር ይወጣና ወደ ቀርቃ ይታጠፋል፤
4 በአድሞን በኩል አድርጎም ወደ ግብፅ ደረቅ ወንዝ ይገባና መቆሚያው ባሕሩ ይሆናል፤ እንግዲህ በደቡብ በኩል ያለው ወሰናቸው ይህ ነው።
5 በምሥራቅ በኩል ያለው ወሰናቸው ደግሞ የጨው ባሕር ሲሆን፣ ይህም የዮርዳኖስ ወንዝ እስከሚሠርግበት ይደርሳል።በሰሜን በኩል ያለው ወሰንም የዮርዳኖስ ወንዝ ከሚሠርግበት የባሕር ወሽመጥ ይነሣና
6 ሽቅብ ወደ ቤትሖግላ ይወጣል፤ ከዚያም በሰሜናዊው ቤትዓረባ በኩል አድርጎ የሮቤል ልጅ የቦሀን ድንጋይ እስካለበት ይደርሳል።