ኢያሱ 17:6-12 NASV

6 የምናሴ ነገድ ሴት ልጆች ከወንዶቹ ጋር ርስት ተካፍለዋልና፤ የገለዓድ ምድር ግን ለቀሩት የምናሴ ዘሮች ተሰጠ።

7 የምናሴ ርስት ከአሴር አንሥቶ ከሴኬም በስተ ምሥራቅ እስካለችው እስከ ሚክምታት ይደርሳል፤ ድንበሩም ወደ ደቡብ በመዝለቅ በዓይንታጱዋ የሚኖረውን ሕዝብ ይጨምራል።

8 የታጱዋ ምድር የምናሴ ይዞታ ነበር፤ ይሁን እንጂ በድንበሩ ላይ የምትገኘው የታጱዋ ከተማ የኤፍሬም ዘሮች ይዞታ ነበረች፤

9 ከዚያም በመቀጠል ድንበሩ በደቡብ በኩል ወደ ቃና ወንዝ ይደርሳል። በምናሴ ከተሞችም መካከል የኤፍሬም ከተሞች ነበሩ፤ ያም ሆኖ የምናሴ ድንበር የወንዙ ሰሜናዊ ክፍል ሲሆን፣ እስከ ባሕሩ ይዘልቃል።

10 በደቡብ በኩል ያለው ምድር የኤፍሬም ሲሆን፣ በሰሜን በኩል ያለው ደግሞ የምናሴ ነበር፤ የምናሴ ግዛት እስከ ባሕሩ የሚደርስ ሲሆን፣ ሰሜናዊ ድንበሩ አሴር፣ ምሥራቃዊ ድንበሩ ደግሞ ይሳኮር ነው።

11 እንዲሁም በይሳኮርና በአሴር ውስጥ፤ ቤትሳን፣ ይብልዓም፣ የዶር ሕዝብ፣ ዓይን ዶር፣ ታዕናክና መጊዶ በዙሪያቸው ካሉ ሰፈሮቻቸው ጋር የምናሴ ነበሩ፤ ሦስተኛውም ናፎት ነው።

12 ይሁን እንጂ የምናሴ ዘሮች እነዚህን ከተሞች መያዝ አልቻሉም፤ ከነዓናውያን የያዙትን ላለመልቀቅ ቊርጥ ሐሳብ አድርገው ነበርና።