ኢያሱ 2:15-21 NASV

15 መኖሪያ ቤቷ የከተማውን ቅጥር ተጠግቶ የተሠራ ስለ ነበር፣ ሰዎቹን በመስኮት አሾልካ በገመድ አወረደቻቸው።

16 እርሷም፣ “የሚከታተሏችሁ ሰዎች እንዳያገኟችሁ፣ ወደ ኰረብታዎቹ ሂዱ፤ እነርሱ እስኪመለሱም ድረስ ሦስት ቀን በዚያ ተሸሸጉ፤ ከዚያ በኋላ መንገዳችሁን ትቀጥላላችሁ” አለቻቸው።

17 ሰዎቹም እንዲህ አሏት፤ “ባማልሽን በዚህ መሓላ የምንያዘው፣

18 ወደ ምድሪቱ በገባን ጊዜ፣ ይህን ቀይ ፈትል እኛን ባወረ ድሽበት መስኮት ላይ አስረሽ ካንጠለጠልሽው፣ እንዲሁም አባትሽንና እናትሽን፣ ወንድሞችሽንና የአባትሽን ቤተ ሰዎች ሁሉ ወደ ቤትሽ ካመጣሻቸው ብቻ ነው።

19 ማንም ከቤትሽ ወጥቶ መንገድ ላይ ቢገኝ፣ ደሙ በራሱ ላይ ነው፤ እኛ አንጠየቅበትም፤ ነገር ግን ከአንቺ ጋር እቤት ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ከተነካ የደሙ ባለ ዕዳ እኛ እንሆናለን።

20 እኛ የምናደርገውን ብትናገሪ ግን፣ ካስማልሽን መሐላ ነጻ እንሆናለን።”

21 እርሷም፣ “ይሁን፤ ባላችሁት ተስማምቻለሁ” ስትል መለሰች፤ ከዚያም ሰደደቻቸው፤ እነርሱም ሄዱ፤ ቀይ ፈትሉንም በመስኮቷ ላይ አንጠለጠለችው።