1 ከዚያም እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤
2 “በሙሴ በኩል በነገርኋችሁ መሠረት የመማጠኛ ከተሞች እንዲለዩ ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤
3 ሳያስበው ድንገት ሰው የገደለ ማንኛውም ሰው ወደዚያ በመሸሽ ከደም ተበቃዩ እንዲያመልጥ ከተማዪቱ መጠለያ ትሁን።
4 “ገዳዩ ከነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ በሚሸሽበት ጊዜ፣ በከተማዪቱ መግቢያ በር ላይ ቆሞ ጒዳዩን ለከተማዪቱ ሽማግሌዎች ይንገራቸው፤ ከዚያም እነርሱ ወደ ከተማቸው አስገብተው የሚኖርበትን ስፍራ ሰጥተውት አብሮአቸው ይቀመጥ።
5 ደም ተበቃዩ ተከታትሎት ቢመጣ፣ ሆን ብሎና በክፋት ተነሣሥቶ ወንድሙን የገደለው ባለመሆኑ፣ ሰዎቹ ነፍሰ ገዳዩን አሳልፈው አይስጡት።
6 በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቀርብና በዚያ ጊዜ የሚያገለግለው ሊቀ ካህናት እስኪሞት ድረስ በዚያች ከተማ ይቆይ። ከዚያም ወደ ቤቱ፣ ሸሽቶ ወደ መጣበት ከተማ ሊመለስ ይችላል።”