14 ከእርሱም ጋር እያንዳንዱን የእስራኤልን ነገድ የሚወክሉ ዐሥር አለቆች አብረው ላኩ፤ እነዚህም እያንዳንዳቸው ከእስራኤላውያን ጐሣዎች የተውጣጡ የየቤተ ሰቡ አለቆች ነበሩ።
15 እነርሱም በገለዓድ ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤላውያን፣ ወደ ጋዳውያንና ወደ ምናሴ ነገድ እኩሌታ ሄደው እንዲህ አሏቸው፤
16 “መላው የእግዚአብሔር ጉባኤ እንዲህ ይላል፤ ‘በእስራኤል አምላክ ላይ እንዲህ ያለ ክህደት የፈጸማችሁት ለምንድን ነው? እግዚአብሔርን ከመከተልስ እንዴት ወደ ኋላ ትላላችሁ? እንዴትስ ዛሬ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፃችሁ ለራሳችሁ መሠዊያ ትሠራላችሁ?
17 በፌጎር የተሠራው ኀጢአት አይበቃንምን? ምንም እንኳ በእግዚአብሔር ጉባኤ ላይ መቅሠፍት ቢወርድም፣ እስከ ዛሬዪቱ ዕለት ድረስ ራሳችንን ከዚያች ኀጢአት አላነጻንም።
18 እናንተ፣ አሁንም እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ ትላላችሁን?“ ‘ዛሬ እናንተ በእግዚአብሔር ላይ ብታምፁ፣ እርሱ ደግሞ ነገ በመላው እስራኤል ጉባኤ ላይ ይቈጣል።
19 የወረሳችኋት ምድር ረክሳ እንደሆነ፣ የእግዚአብሔር ማደሪያ ወደ ተተከለበት ወደ እግዚአብሔር ምድር መጥታችሁ ከእኛ ጋር ርስት ተካፈሉ፤ ነገር ግን ከአምላካችን ከእግዚአብሔር መሠዊያ በስተቀር ሌላ መሠዊያ ሠርታችሁ በእግዚአብሔርም ሆነ በእኛ ላይ አታምፁ።
20 የዛራ ልጅ አካን፣ እርም የሆነውን ነገር በመውሰድ ኀጢአት ስለ ሠራ፣ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ላይ ቍጣ አልመጣምን? በሠራው ኀጢአት የሞተውም እርሱ ብቻ አልነበረም።”