ኢያሱ 23:11-16 NASV

11 ስለዚህ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለመውደድ ተጠንቀቁ።

12 ነገር ግን ከእርሱ ተመልሳችሁ ተርፈው በመካከላችሁ ከሚገኙት ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር ብትተባበሩ፣ በጋብቻም ብትተሳሰሩና ብትቀላቀሉ፣

13 አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእንግዲህ ከፊታችሁ እንደማያወጣቸው ይህን ልታውቁ ይገባል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድር እስክትጠፉ ድረስም ወጥመድና አሽክላ፣ ለጀርባችሁ ጅራፍ፣ ለዐይኖቻችሁም እሾኽ ይሆኑባችኋል።

14 “እነሆ፤ አሁን የምድርን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ በፍጹም ልባችሁ በፍጹም ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።

15 ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር የሰጣችሁ መልካሙ ተስፋ በሙሉ እንደ ተፈጸመ ሁሉ፣ እንደዚሁም አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር እስኪያጠፋችሁ ድረስ ክፉውን ነገር ያመጣባችኋል።

16 አምላካችሁ እግዚአብሔር ያዘዛችሁን ኪዳን ብታፈርሱ፣ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታገለግሉና ብትሰግዱላቸው የእግዚአብሔር ቊጣ በላያችሁ ይነዳል፤ ከሰጣችሁም ከመልካሚቱ ምድር በፍጥነት ትጠፋላችሁ።”