1 ከዚያም ኢያሱ የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ በሴኬም ሰበሰበ፤ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች፣ መሪዎች፣ ፈራጆችና ሹማምት ጠራ፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ።
2 ኢያሱም ሕዝቡን ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የቀድሞ አባቶቻችሁ፣ የአብርሃምንና የናኮርን አባት ታራን ጨምሮ ከብዙ ዘመን በፊት ከወንዙ ማዶ ኖሩ፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ።
3 እኔ ግን አባታችሁን አብርሃምን ከወንዙ ማዶ ካለው ምድር አምጥቼ፣ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሮቹን አበዛሁለት፤ ይስሐቅንም ሰጠሁት።
4 ለይስሐቅ ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም ኰረብታማውን የሴይርን ምድር ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ያዕቆብና ልጆቹ ግን ወደ ግብፅ ወረዱ።