1 ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፤ ከእስራኤላውያንም ሁሉ ጋር ከሰጢም ወደ ዮርዳኖስ መጥተው፣ ወንዙን ከመሻገራቸው በፊት በዚያ ሰፈሩ።
2 ከሦስት ቀን በኋላም የጦሩ አለቆች በሰፈር ውስጥ አለፉ፤
3 ሕዝቡንም እንዲህ ሲሉ አዘዙ፤ “ሌዋውያን ካህናቱ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው ስታዩ፣ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ታቦቱን ተከተሉ፤
4 ካሁን በፊት በዚህ መንገድ ሄዳችሁ ስለማታውቁ፤ በየት በኩል መሄድ እንዳለባችሁ በዚህ ትረዳላችሁ፤ ሆኖም በታቦቱና በእናንተ መካከል የሁለት ሺህ ክንድ ያህል ርቀት ይኑር፤ ወደ ታቦቱም አትቅረቡ።”