ኢያሱ 3:3-9 NASV

3 ሕዝቡንም እንዲህ ሲሉ አዘዙ፤ “ሌዋውያን ካህናቱ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው ስታዩ፣ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ታቦቱን ተከተሉ፤

4 ካሁን በፊት በዚህ መንገድ ሄዳችሁ ስለማታውቁ፤ በየት በኩል መሄድ እንዳለባችሁ በዚህ ትረዳላችሁ፤ ሆኖም በታቦቱና በእናንተ መካከል የሁለት ሺህ ክንድ ያህል ርቀት ይኑር፤ ወደ ታቦቱም አትቅረቡ።”

5 ከዚያም ኢያሱ ሕዝቡን፣ “በነገው ዕለት እግዚአብሔር በመካከላችሁ አስደናቂ ነገር ስለሚያደርግ ራሳችሁን ቀድሱ” አላቸው።

6 ኢያሱም ካህናቱን፣ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ ሕዝቡን ቀድማችሁ ሂዱ” አላቸው፤ እነርሱም ታቦቱን ተሸክመው ሕዝቡን ቀድመው ሄዱ።

7 እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ ሁሉ፣ ከአንተም ጋር መሆኔን ያውቁ ዘንድ፣ በእስራኤል ሁሉ ፊት አንተን ከፍ ከፍ ማድረጌን በዛሬዋ ዕለት እጀምራለሁ።

8 የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸከሙትንም ካህናት፣ ‘ከዮርዳኖስ ውሃ ዳር ስትደርሱ፣ በወንዙ ውስጥ ገብታችሁ ቁሙ’ በላቸው።”

9 ኢያሱ የእስራኤልን ሕዝብ “ወደዚህ ቀርባችሁ፣ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ አላቸው፤