ኢያሱ 4:3-9 NASV

3 እንዲሁም ከዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ልክ ካህናቱ ከቆሙበት ስፍራ ዐሥራ ሁለት ድንጋይ አንሥተው በመሸከም ከእናንተ ጋር እንዲሻገሩና ዛሬ በምታድሩበት ቦታ እንዲያኖሯቸው ንገራቸው።”

4 ስለዚህ ኢያሱ ከእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ የሾማቸውን ዐሥራ ሁለት ሰዎች ጠራ፤

5 እንዲህም አላቸው፤ “ከአምላካችሁ ከእግዚአብሔር ታቦት ፊት ቀድማችሁ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ዕለፉ፤ እያንዳንዳችሁም በእስራኤል ነገድ ቊጥር አንዳንድ ድንጋይ በትከሻችሁ ተሸከሙ፤

6 ይህም በመካከላችሁ ምልክት እንዲሆናችሁ ነው። ወደ ፊት ልጆቻችሁ፣ ‘እነዚህ ድንጋዮች ምንድን ናቸው?’ ብለው ቢጠይቋችሁ፣

7 የዮርዳኖስ ወንዝ በእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት መቆሙን፤ እንዲሁም ታቦቱ ዮርዳኖስን በሚሻገርበት ጊዜ፣ የዮርዳኖስ ወንዝ ውሃ መቆሙን፣ እነዚህ ድንጋዮች ለእስራኤል ሕዝብ የዘላለም መታሰቢያ መሆናቸውን ንገሯቸው።”

8 እስራኤላውያንም ኢያሱ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ እግዚአብሔር ለኢያሱ በነገረውም መሠረት፣ በእስራኤል ነገዶች ቊጥር ልክ ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ከዮርዳኖስ ወንዝ መካከል አነሡ፤ ወደ ሰፈራቸውም ይዘው በመሻገር በዚያ አኖሯቸው።

9 ኢያሱም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ቆመውበት በነበረው በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ሌሎች ዐሥራ ሁለት ድንጋዮችን አቆመ፤ እነዚህም ድንጋዮች እስከ ዛሬ ድረስ በዚሁ ስፍራ ይገኛሉ።