ኢያሱ 6:13-19 NASV

13 ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እየሄዱ፣ መለከቱን ባለማቋረጥ ይነፉ ጀመር፤ የታጠቁ ተዋጊዎችም እነዚህን በመቅደም ሲሄዱ፣ የደጀን ጠባቂዎቹ ደግሞ የእግዚአብሔርን ታቦት ይከተሉ ነበር፤ ካህናቱም ሳያቋርጡ መለከት ይነፉ ነበር።

14 በሁለተኛውም ቀን ከተማዪቱን አንድ ጊዜ ከዞሩ በኋላ ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀን ሙሉም እንዲሁ አደረጉ።

15 በሰባተኛው ቀን ገና ጎሕ ሲቀድ ተነሡ፤ እንደ በፊቱም ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ የዞሯትም በዚያን ቀን ብቻ ነው።

16 በሰባተኛው ዙር ላይ ካህናቱ መለከቱን ሲነፉ፣ ኢያሱ ሕዝቡን እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “እግዚአብሔር ይህችን ከተማ ሰጥቶአችኋልና ጩኹ

17 ከተማዪቱና በውስጧ ያለው ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ስለ ሆነ ፈጽማችሁ አጥፉ፣ እኛ የላክናቸውን ሰላዮች ስለሸሸገች ጋለሞታዪቱ ረዓብ ብቻና ከእርሷ ጋር በቤቷ ውስጥ ያሉት ሁሉ ይትረፉ።

18 እናንተ ግን እርም ከሆኑት ነገሮች አንዳች በመውሰድ በራሳችሁ ላይ ጥፋት እንዳታመጡ እጃችሁን ሰብስቡ፤ ያለዚያ የእስራኤልን ሰፈር ለጥፋት ትዳርጋላችሁ፤ ክፉ ነገር እንዲደርስበትም ታደርጋላችሁ፤

19 ብሩና ወርቁ እንዲሁም የናሱና የብረቱ ዕቃ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ስለ ሆነ፣ ወደ እግዚአብሔር ግምጃ ቤት ይግባ።”