2 እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ ኢያሪኮን ከንጉሥዋና ከተዋጊዎቿ ጋር አሳልፌ በእጅህ ሰጥቻለሁ።
3 ከተማዪቱን ከተዋጊዎቻችሁ ጋር አንድ ጊዜ ዙሩ፤ ይህንም ስድስት ቀን አድርጉ።
4 ሰባት ካህናት፣ ሰባት ቀንደ መለከት ተሸክመው በታቦቱ ፊት ይውጡ፤ በሰባተኛውም ቀን ካህናቱ መለከት እየነፉ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ይዙሩ።
5 የማያቋርጥ የመለከት ድምፅ ሲነፋ በምትሰሙበት ጊዜ፣ ሕዝቡ ሁሉ ከፍ ያለ ጩኸት ያሰማ፤ ከዚያም የከተማዪቱ ቅጥር ይፈርሳል፤ ሕዝቡም ወደ ላይ ይወጣል፤ እያንዳንዱም ሰው በቀጥታ ይገባል።”
6 ስለዚህ የነዌ ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ፣ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸከሙ፤ ሰባት ካህናትም ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ” አላቸው።
7 ሕዝቡንም፣ “ወደ ፊት ሂዱ፤ ከተማዋን ዙሩ፤ የታጠቁ ተዋጊዎችም በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ቀድመው ይሂዱ፤ ከተማዪቱንም ዙሩ” ሲል አዘዛቸው።
8 ኢያሱም ለሕዝቡ ከተናገረ በኋላ፣ ሰባቱ ካህናት በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው መለከታቸውን እየነፉ ወደ ፊት ቀደሙ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦትም ተከተላቸው።