ኢያሱ 6:9-15 NASV

9 የታጠቁ ተዋጊዎችም መለከት ከሚነፉት ካህናት ፊት ቀድመው ሲሄዱ፣ ደጀን የሆኑት ጠባቂዎች ደግሞ ታቦቱን ተከተሉ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ መለከቶቹ ባለማቋረጥ ይነፉ ነበር።

10 ኢያሱ ሕዝቡን፣ “የማሸበሪያ ጩኸት አታሰሙ፤ ድምፃችሁ ከፍ ብሎ አይሰማ፤ ጩኹ እስከምላችሁም ቀን ድረስ ከአፋችሁ አንዲት ቃል አትውጣ፤ የምትጮኹት ከዚያ በኋላ ነው” ሲል አዘዛቸው።

11 ስለዚህ ኢያሱ የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸክመው፣ ከተማዪቱን አንድ ጊዜ እንዲዞሩ አደረገ። ከዚያም ሕዝቡ ወደ ሰፈር ተመልሰው ዐደሩ።

12 ኢያሱ በማግሥቱ ማልዶ ተነሣ፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸከሙ።

13 ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እየሄዱ፣ መለከቱን ባለማቋረጥ ይነፉ ጀመር፤ የታጠቁ ተዋጊዎችም እነዚህን በመቅደም ሲሄዱ፣ የደጀን ጠባቂዎቹ ደግሞ የእግዚአብሔርን ታቦት ይከተሉ ነበር፤ ካህናቱም ሳያቋርጡ መለከት ይነፉ ነበር።

14 በሁለተኛውም ቀን ከተማዪቱን አንድ ጊዜ ከዞሩ በኋላ ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀን ሙሉም እንዲሁ አደረጉ።

15 በሰባተኛው ቀን ገና ጎሕ ሲቀድ ተነሡ፤ እንደ በፊቱም ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ የዞሯትም በዚያን ቀን ብቻ ነው።