ኢያሱ 7:14-20 NASV

14 “ ‘ማለዳ በየነገድ በየነገዳችሁ ሆናችሁ ቅረቡ፤ እግዚአብሔር የሚለየው ነገድ በየጐሣ በየጐሣው ሆኖ ከሕዝቡ መካከል ወደ ፊት ይወጣል፤ እንዲሁም እግዚአብሔር የሚለየው ጐሣ በየቤተ ሰቡ ሆኖ ወደ ፊት ይወጣል፤ እግዚአብሔር የሚለየው ቤተ ሰብ ደግሞ በግለሰብ በግለሰብ ሆኖ ወደ ፊት ይወጣል።

15 እርሙ የተገኘበት ሰው፣ እርሱና ያለው ሁሉ በእሳት ይቃጠላል፤ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን አፍርሶአል፤ በእስራኤልም ዘንድ አሳፋሪ ተግባር ፈጽሞአልና።”

16 በማግሥቱ ጥዋት ኢያሱ ማልዶ ተነሣ፤ እስራኤልንም በየነገድ በየነገዳቸው ሆነው እንዲቀርቡ አደረገ፤ ከዚያም የይሁዳ ነገድ ተለየ፤

17 የይሁዳንም ጐሣዎች ወደ ፊት አቀረበ፤ ከእነዚህም የዛራን ጐሣ ለየ፤ እነዚህን ደግሞ በየቤተ ሰባቸው እንዲወጡ አደረገ፤ ከእነዚህም ዘንበሪ ተለየ።

18 ኢያሱ የዘንበሪን ቤተ ሰብ አባላት አንድ በአንድ ወደ ፊት እንዲቀርቡ አደረገ፤ ከዚያም ከይሁዳ ነገድ የሆነውም የዛራ ልጅ፣ የዘንበሪ ልጅ፣ የከርሚ ልጅ አካን ለብቻው ተለየ።

19 ኢያሱም አካንን፣ “ልጄ ሆይ፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጥ፤ ለእርሱም ተናዘዝ፤ ያደረግኸውን ሳትደብቅ ንገረኝ” አለው።

20 አካንም መልሶ ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “እውነት ነው! የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በድያለሁ፤ ያደረግሁትም ይህ ነው፤