ኢያሱ 7:9-15 NASV

9 ከነዓናውያንና ሌሎቹ የምድሪቱ ነዋሪዎች ሁሉ ይህን ሲሰሙ ይከቡናል፤ ስማችንንም ከምድር ገጽ ያጠፉታል፤ እንግዲህ ስለ ታላቁ ስምህ ስትል የምታደርገው ምንድን ነው?”

10 እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ተነሥ! ለምን በግንባርህ ተደፋህ?

11 እስራኤል በድሎአል፤ እንዲጠብቁ ያዘዝኋቸውን ቃል ኪዳኔን ጥሰዋል፤ እርም የሆነውን ነገር ወስደዋል፤ ሰርቀዋል፤ ዋሽተዋል፤ የወሰዱትንም ከራሳቸው ንብረት ጋር ደባልቀዋል።

12 እንግዲህ እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን ለመቋቋም ያልቻሉት በዚህ ምክንያት ነው። ጀርባቸውን አዙረው የሸሹትም ለጥፋት በመዳረጋቸው ነው። እርም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ፣ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አልሆንም።

13 “ተነሣ፤ ሕዝቡን ቀድስ፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እስራኤል ሆይ፤ እርም የሆነ ነገር በመካከላችሁ ስላለ፣ ይህን ካላስወገዳችሁ ጠላቶቻችሁን ለመቋቋም እንደማትችሉ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና ለነገ ራሳችሁን ለማዘጋጀት ሰውነታችሁን ቀድሱ።

14 “ ‘ማለዳ በየነገድ በየነገዳችሁ ሆናችሁ ቅረቡ፤ እግዚአብሔር የሚለየው ነገድ በየጐሣ በየጐሣው ሆኖ ከሕዝቡ መካከል ወደ ፊት ይወጣል፤ እንዲሁም እግዚአብሔር የሚለየው ጐሣ በየቤተ ሰቡ ሆኖ ወደ ፊት ይወጣል፤ እግዚአብሔር የሚለየው ቤተ ሰብ ደግሞ በግለሰብ በግለሰብ ሆኖ ወደ ፊት ይወጣል።

15 እርሙ የተገኘበት ሰው፣ እርሱና ያለው ሁሉ በእሳት ይቃጠላል፤ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን አፍርሶአል፤ በእስራኤልም ዘንድ አሳፋሪ ተግባር ፈጽሞአልና።”