ኢያሱ 8:19-25 NASV

19 ይህን እንዳደረገም ያደፈጡት ሰዎች ከተደበቁበት ስፍራ በፍጥነት ወጥተው ወደ ፊት ሮጡ፤ ገብተው ከተማዪቱን ያዟት፤ ወዲያውኑም በእሳት አቃጠሏት።

20 የጋይ ሰዎች ወደ ኋላ ዞረው ሲመለከቱ የከተማዪቱ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፤ ወደ ምድረ በዳ ይሸሹ የነበሩት እስራኤላውያን ፊታቸውን ስላዞሩባቸውም፣ በየትኛውም በኩል ማምለጫ መንገድ አልነበራቸውም።

21 ኢያሱና እስራኤል ሁሉ ያደፈጠው ጦር ከተማዪቱን መያዙንና ጢሱ ወደ ላይ መውጣቱን ሲያዩ፣ ወደ ኋላ ተመልሰው በጋይ ሰዎች ላይ አደጋ ጣሉባቸው፤

22 ያደፈጡትም ሰዎች እንደዚሁ ከከተማዪቱ ወጥተው መጡባቸው፤ ስለዚህ እስራኤላውያን በዚያም በዚህም ስለ ከበቧቸው የጋይን ሰዎች ከመካከል አደረጓቸው፤ እስራኤላውያንም ሰዎቹን ፈጇቸው፤ አንድ እንኳ የተረፈ ወይም ያመለጠ አልነበረም፤

23 ነገር ግን የጋይን ንጉሥ ከነሕይወቱ ይዘው ወደ ኢያሱ አመጡት።

24 እስራኤላውያን የጋይን ወንዶች ሁሉ ባሳደዷቸው ሜዳና ምደረ በዳ ከጨረሷቸውና እያንዳንዳቸውንም በሰይፍ ከፈጁ በኋላ፣ ወደ ከተማዪቱ ተመልሰው በዚያ ያገኙትን ሁሉ ገደሉ።

25 በዚያች ዕለት የጋይ ሰዎች ሁሉ አለቁ፤ የወንዶቹና የሴቶቹም ብዛት ዐሥራ ሁለት ሺህ ነበር።