ኢያሱ 9:15-21 NASV

15 ኢያሱም በሰላም ለመኖር የሚያስችላቸውን ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደረገ፤ የጉባኤውም መሪዎች ይህንኑ በመሓላ አጸኑላቸው።

16 እስራኤላውያን ከገባዖን ሰዎች ጋር ቃል ኪዳኑን ካደረጉ ከሦስት ቀን በኋላ፣ ሰዎቹ እዚያው አጠገባቸው የሚኖሩ ጎረቤቶቻቸው መሆናቸውን ሰሙ።

17 ስለዚህ እስራኤላውያን ተጒዘው በሦስተኛው ቀን ገባዖን፣ ከፊራ፣ ብኤሮትና ቂርያትይዓይሪም ወደተባሉት የገባዖን ሰዎች ወደሚኖሩባቸው ከተሞች መጡ።

18 ሆኖም እስራኤላውያን አልወጓቸውም፤ የጉባዔው መሪዎች በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ምለውላቸው ነበርና።ማኅበሩም ሁሉ በመሪዎቹ ላይ አጒረመረሙ፤

19 ነገር ግን መሪዎቹ ሁሉ ለማኅበሩ እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ ‘በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ስለማልንላቸው፣ አሁን ጒዳት ልናደርስባቸው አንችልም፤

20 እንዲህ እናደርግላቸዋለን፤ የገባንላቸውን መሓላ በማፍረስ ቊጣ እንዳይደርስብን፣ በሕይወት እንዲኖሩ እንዲሁ እንተዋቸዋለን፤

21 ነገር ግን ለማኅበረ ሰቡ በሙሉ ዕንጨት እየቈረጡ ውሃ እየቀዱ ይኑሩ።” ስለዚህ መሪዎቹ የገቡላቸው ቃል ተጠበቀ።