ዘዳግም 11:11-17 NASV

11 ዮርዳኖስን ተሻግረህ ልትወርሳት ያለችው ምድር ግን፣ ከሰማይ ዝናብ የምትጠጣ፣ ተራሮችና ሸለቆች ያሉባት ምድር ናት።

12 ይህች ምድር አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚንከባከባት፣ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ የአምላክህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ዐይን ምንጊዜም የማይለያት ናት።

13 ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዞች በታማኝነት ብትጠብቁ፣ ይኸውም አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ብትወዱና በፍጹም ልባችሁ፣ በፍጹም ነፍሳችሁም እርሱን በማገልገል በታማኝነት ብትጠብቁ፣

14 እህልህን፣ ወይንህንና ዘይትህን እንድትሰበስብ የበልጉንና የክረምቱን ዝናብ በምድርህ ላይ በየወቅቱ አዘንባለሁ።

15 በሜዳ ላይ ለከብቶችህ ሣር እሰጣለሁ፤ አንተም ትበላለህ፤ ትጠግባለህም።

16 ተጠንቀቁ አለበለዚያ ተታላችሁ ሌሎች አማልክትን ታመልካላችሁ፤ ትሰግዳላችሁም።

17 ከዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቊጣ በላያችሁ ይነዳል፤ እርሱም ዝናብ እንዳይዘንብ፣ ምድሪቱም ፍሬ እንዳትሰጥ ሰማያትን ይዘጋል፤ እናንተም እግዚአብሔር (ያህዌ) ከሚሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር ወዲያውኑ ትጠፋላችሁ።