ዘዳግም 29:20-26 NASV

20 እግዚአብሔር (ያህዌ) ለዚያ ሰው ፈጽሞ ይቅርታ አያደርግለትም፤ ቊጣውና ቅናቱ በእርሱ ላይ ይነድበታል። በዚህ መጽሐፍ የተጻፈው ርግማን ሁሉ ይወርድበታል፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ስሙን ከሰማይ በታች ይደመስሰዋል።

21 በዚህ የሕግ መጽሐፍ በተጻፈው የኪዳኑ ርግማን መሠረት፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) እርሱን ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ለጥፋት ይለየዋል።

22 የሚቀጥለው ትውልድ ከእናንተ በኋላ የሚተኩት ልጆቻችሁና ከሩቅ አገር የሚመጡ እንግዶች በምድሪቱ የደረሰውን ታላቅ መቅሠፍትና እግዚአብሔር (ያህዌ) ያመጣባቸውን በሽታዎች ያያሉ።

23 ምድሪቱ በሙሉ የተቃጠለ ጨውና ዲን ዐመድ ትሆናለች። አንዳች ነገር አይተከልባትም፤ ምንም ነገር አያቈጠቊጥባትም፤ የሚያድግ ተክል አይገኝባትም። የሚደርስባት ውድመት እግዚአብሔር (ያህዌ) በታላቅ ቊጣ እንደ ገለባበጣቸው እንደ ሰዶምና ገሞራ፣ እንደ አዳማና ሲባዮ ጥፋት ይሆናል።

24 አሕዛብም ሁሉ፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚች ምድር ላይ ይህን ለምን አደረገባት? ይህ አስፈሪና የሚነድ ቊጣስ ለምን መጣባት?” ብለው ይጠይቃሉ።

25 መልሱም፣ “የአባቶቻቸው አምላክ (ኤሎሂም) ከግብፅ ምድር ባወጣቸው ጊዜ፣ ከእነርሱ ጋር የገባውን ኪዳን ሕዝቡ ስለ ተዉ ነው።

26 ወጥተውም የማያውቋቸውን፣ እርሱም ያላዘዛቸውን ሌሎችን አማልክት አመለኩ፤ ሰገዱላቸውም።