ዘዳግም 5:21-27 NASV

21 “የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ። በባልንጀራህ ቤትም ሆነ በመሬቱ፣ በወንድ ሆነ በሴት አገልጋዩ፣ በበሬውም ሆነ በአህያው ወይም የእርሱ በሆነው ነገር ላይ ዐይንህን አትጣል።”

22 እግዚአብሔር (ያህዌ) በተራራው ላይ በእሳቱ፣ በደመናውና በድቅድቁ ጨለማ ውስጥ ለማኅበራችሁ ሁሉ በከፍተኛ ድምፅ የተናገራችሁ ትእዛዛቱ እነዚህ ናቸው፤ የጨመረውም ሌላ የለም፤ ትእዛዛቱንም በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጽፎ ሰጠኝ።

23 ተራራው በእሳት ሲቃጠል፣ ከጨለማው ውስጥ ድምፁን በሰማችሁ ጊዜ እናንተ የየነገዶቻችሁ አለቆችና ሽማግሌዎቻችሁም በሙሉ ወደ እኔ ዘንድ መጣችሁ፤

24 እንዲህም አላችሁ፤ “አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ክብሩንና ግርማውን አሳይቶናል፤ ከእሳቱም ውስጥ ድምፁን ሰምተናል። እግዚአብሔር አነጋግሮትም እንኳ፣ ሰው በሕይወት ሊኖር እንደሚችል በዛሬው ቀን አይተናል።

25 ከእንግዲህ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ድምፅ ብንሰማ እንሞታለን፤ ይህችም ታላቅ እሳት ፈጽማ ታጠፋናለች፤ ታዲያ ለምን እንሙት?

26 ለመሆኑ ከእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር እኛ እንደ ሰማነው ሁሉ፣ የሕያው እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ድምፅ ሰምቶ በሕይወት ለመኖር የቻለ ከሥጋ ለባሽ ማን አለ?

27 አንተ ቅረብ፤ አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚለውን ሁሉ አዳምጥ፤ ከዚያም አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚነግርህን ሁሉ ንገረን፤ እኛም እንሰማለን፤ እናደርገዋለንም።”