1 በሕይወት እንድትኖሩ፣ እንድትበዙና እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአባቶቻችሁ በመሐላ ተስፋ የገባላቸውን ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱ፣ ዛሬ እኔ የምሰጥህን እያንዳንዱን ትእዛዝ ለመከተል ጥንቃቄ አድርጉ።
2 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞቹን መጠበቅህንና በልብህ ያለውን ለማወቅ፣ ትሑት ሊያደርግህና ሊፈትንህ በእነዚህ አርባ ዓመታት በዚህ ምድረ በዳ ጒዞህ ሁሉ እንዴት እንደ መራህ አስታውስ።
3 ሰው ከእግዚአብሔር (ያህዌ) አፍ በሚወጣው በእያንዳንዱ ቃል እንጂ፣ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ሊያስተምርህ አስራበህ፤ አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቁትን መና መገበህ፤
4 በእነዚህ አርባ ዓመታት ውስጥ ልብስህ አላለቀም፤ እግርህም አላበጠም።
5 ስለዚህ ሰው ልጁን እንደሚቀጣ፣ አምላክህ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም ያህዌ) አንተን እንደሚ ቀጣህ በልብህ ዕወቅ።
6 በመንገዶቹ በመሄድና እርሱንም በማክበር፣ የአምላክህን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞች ጠብቅ።