1 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ተመልሰህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እነዚህን ታምራዊ ምልክቶች በመካከላቸው ለማድረግ የፈርዖንንና የሹማምቱን ልብ አደንድኛለሁና፤
2 ይኸውም ግብፃውያንን እንዴት አድርጌ እንደ ቀጣኋቸውና በመካከላቸውም ምልክቶቼን እንዴት እንዳደረግሁ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ እንድትነግሩና እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኔንም እንድታውቁ ነው።”
3 ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እንዲህ አሉት፤ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንዲህ ይላል፤ ‘ራስህን በፊቴ ለማዋረድ እስከ መቼ እምቢ ትላለህ? ሕዝቤ ያመልኩኝ ዘንድ ልቀቃቸው።
4 እንዳይሄዱ ብትከለክላቸው ነገ በአገርህ ላይ አንበጣዎችን አመጣለሁ።
5 አንበጣዎቹም ምድሪቱ እስከማትታይ ድረስ ይሸፍኗታል፤ በመስክህ ላይ እያቈጠቈጠ ያለውን ዛፍ ሁሉ ሳይቀር ከበረዶ የተረፈውንም ጥቂቱን ሁሉ ይበሉታል።
6 የአንተን፣ የሹማምትህንና የግብፃውያንን ቤቶች ሁሉ ይሞሏቸዋል፤ ይህም አባቶችህም ሆኑ ቅድመ አያቶችህ በዚህች ምድር ከሰፈሩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከቶ አይተውት የማያውቁት ነው።’ ” ሙሴም ተመለሰና ከፈርዖን ተለይቶ ሄደ።