ዘፀአት 12:13-19 NASV

13 ደሙም ያላችሁበትን ቤት ለይቶ የሚያሳይ ምልክት ይሆንላችኋል፤ እኔ ደሙን በማይበት ጊዜ እናንተን አልፋለሁ፤ ግብፅን ስቀጣ መቅሠፍቱ አይደርስባችሁም።

14 “ይህን ቀን መታሰቢያ ታደርጉታላችሁ፤ በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ ቋሚ ሥርዐት ሆኖ የእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል አድርጋችሁ ታከብሩታላችሁ።

15 ለሰባት ቀናት እርሾ የሌለበትን ቂጣ ብሉ፤ በመጀመሪያው ቀን እርሾን ሁሉ ከቤታችሁ አስወግዱ፤ በነዚህ ሰባት ቀናት እርሾ ያለበትን ቂጣ የበላ ማንኛውም ሰው ከእስራኤል ይወገድ።

16 በመጀመሪያውና በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባዔ አድርጉ። በእነዚህ ቀናት ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩ፤ የምትሠሩት ሥራ ቢኖር ለእያንዳንዱ ምግብ ማዘጋጀት ብቻ ይሆናል።

17 የቂጣን በዓል አክብሩ፤ ሰራዊታችሁን ከግብፅ ምድር ያወጣሁት በዚች ዕለት ነውና። ይህን ዕለት ለሚቀጥለው ትውልድ ቋሚ ሥርዐት በማድረግ አክብሩት።

18 ከመጀመሪያው ወር ከአሥራ አራተኛው ቀን ምሽት እስከ ሃያ አንደኛው ቀን ምሽት ድረስ እርሾ የሌለበት ያልቦካ ቂጣ ትበላላችሁ።

19 ለሰባት ቀን እርሾ በቤታችሁ አይኑር፤ መጻተኛም ሆነ የአገር ተወላጅ እርሾ ያለበትን ቂጣ የበላ ከእስራኤል ማኅበር ይወገድ።