8 ሥጋውንም በዚያችው ሌሊት በእሳት ላይ ጠብሰው ከመራራ ቅጠልና ካልቦካ ቂጣ ጋር ይብሉት።
9 ጥሬውን ሥጋ ወይም ቅቅሉን አትብሉ፤ ነገር ግን ጭንቅላቱን፣ እግሮቹንና ሆድ ዕቃውን በእሳት ላይ ጠብሳችሁ ብሉት።
10 ከሥጋው ተርፎ አይደር፤ ያደረ ቢኖር ግን በእሳት ይቃጠል።
11 ስትበሉም ልብሳችሁን ለብሳችሁ፣ ባጭር ታጥቃችሁ፣ ጫማችሁን አድርጋችሁ በትራችሁን ይዛችሁ በጥድፊያ ብሉት፤ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ፋሲካ ነው።
12 “እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ ምድር ላይ አልፋለሁ፤ ከሰውም ከእንስሳም የተወለደውን የበኵር ልጅ ሁሉ እገድላለሁ፤ የግብፅን አማልክት ሁሉ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
13 ደሙም ያላችሁበትን ቤት ለይቶ የሚያሳይ ምልክት ይሆንላችኋል፤ እኔ ደሙን በማይበት ጊዜ እናንተን አልፋለሁ፤ ግብፅን ስቀጣ መቅሠፍቱ አይደርስባችሁም።
14 “ይህን ቀን መታሰቢያ ታደርጉታላችሁ፤ በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ ቋሚ ሥርዐት ሆኖ የእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል አድርጋችሁ ታከብሩታላችሁ።