1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤
2 “መጀመሪያ የተወለደውን ወንድ ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ፤ ከእስራኤላውያን መካከል የእናቱ የበኵር ልጅ የሆነው ማሕፀን ከፋች ሰውም ሆነ እንስሳ የእኔ ነው።”
3 ከዚያም ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አለ፤ “ከባርነት ምድር ከግብፅ የወጣችሁባትን ይህችን ዕለት አስታውሱ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር (ያህዌ) በኀያል ክንዱ አውጥቶአችኋል። እርሾ ያለበትን ማንኛውንም ነገር አትብሉ።
4 እነሆ በዚች ዕለት በአቢብ ወር ወጥታችኋል።
5 እግዚአብሔር (ያህዌ) ለእናንተ ለመስጠት ሲል ቀድሞ ለአባቶቻችሁ ወደ ማለላቸው ማርና ወተት ወደምታፈሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ኤዊያውያን፣ ኢያቡሳውያን ምድር በምትገቡበት ጊዜ ይህን በዓል በዚህ ወር ታከብራላችሁ።