ዘፀአት 13:1-7 NASV

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤

2 “መጀመሪያ የተወለደውን ወንድ ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ፤ ከእስራኤላውያን መካከል የእናቱ የበኵር ልጅ የሆነው ማሕፀን ከፋች ሰውም ሆነ እንስሳ የእኔ ነው።”

3 ከዚያም ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አለ፤ “ከባርነት ምድር ከግብፅ የወጣችሁባትን ይህችን ዕለት አስታውሱ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር (ያህዌ) በኀያል ክንዱ አውጥቶአችኋል። እርሾ ያለበትን ማንኛውንም ነገር አትብሉ።

4 እነሆ በዚች ዕለት በአቢብ ወር ወጥታችኋል።

5 እግዚአብሔር (ያህዌ) ለእናንተ ለመስጠት ሲል ቀድሞ ለአባቶቻችሁ ወደ ማለላቸው ማርና ወተት ወደምታፈሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ኤዊያውያን፣ ኢያቡሳውያን ምድር በምትገቡበት ጊዜ ይህን በዓል በዚህ ወር ታከብራላችሁ።

6 ለሰባት ቀን ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ትበላላችሁ። በሰባተኛውም ቀን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል ታደርጋላችሁ።

7 በእነዚህም ሶስት ቀናት ያልቦካ ቂጣ ትበላላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ እርሾ ያለበት ነገር ፈጽሞ አይገኝ፤ በምድራችሁም አዋሳኝ በየትኛውም ቦታ እርሾ ፈጽሞ አይኑር።