13 ከአህያ በመጀመሪያ የተወለደውን ውርንጫ ግን በጠቦት ትዋጁታላችሁ፤ አህያውን ካልዋጃችሁት ግን አንገቱን ስበሩት። ከወንድ ልጆቻችሁ መካከል በኵር የሆኑትን ሁሉ ዋጁ።
14 “በሚመጡት ዘመናት ልጅህ፣ ‘ይህ ምን ማለት ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ እንዲህ በለው፤ ‘ከባርነት ምድር ከግብፅ እግዚአብሔር (ያህዌ) በኀያል ክንዱ አወጣን፤
15 ፈርዖን እኛን አለቅም ብሎ ልቡን ባደነደነ ጊዜ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ በኵር ሆኖ በግብፅ የተወለደውን ሁሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) ገደለው። እንግዲህ በመጀመሪያ የእናቱን ማሕፀን የከፈተውን ወንድ ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የምሠዋውና የልጆቼ በኵር ሆኖ የተወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ የምዋጀው በዚህ ምክንያት ነው።
16 እግዚአብሔር (ያህዌ) በኀያል ክንዱ እኛን ከግብፅ ያወጣን ስለ ሆነ ይህ ሥርዐት በእጅህም ሆነ በግንባርህ ላይ እንደ ምልክት ይሆናል።”
17 ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ አቋራጭ ቢሆንም እንኳ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በፍልስጥኤም ምድር በሚያልፈው መንገድ አልመራቸውም “ጦርነት ቢያጋጥማቸው ሐሳባቸውን ለውጠው ወደ ግብፅ ይመለሱ ይሆናል” ብሎአልና።
18 ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሕዝቡን ዙሪያ በሆነው በምድረ በዳው መንገድ ወደ ቀይ ባሕር መራቸው፤ እስራኤላውያንም ለጦርነት ዝግጁ ሆነው ከግብፅ ወጡ።
19 ዮሴፍ፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በእርግጥ ይጐበኛችኋል፤ በዚያን ጊዜም ዐፅሜን ይዛችሁ ከዚች ምድር መውጣት አለባችሁ ብሎ የእስራኤልን ልጆች አስምሎአቸው ስለ ነበር ሙሴ የዮሴፍን ዐፅም ይዞ ወጣ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሕዝቡን ዙሪያ በሆነው በምድረ በዳው መንገድ ወደ ቀይ ባህር መራቸው፤ እስራኤላውያንም ለጦርነት ዝግጁ ሆነው ከግብፅ ወጡ።