ዘፀአት 13:16-22 NASV

16 እግዚአብሔር (ያህዌ) በኀያል ክንዱ እኛን ከግብፅ ያወጣን ስለ ሆነ ይህ ሥርዐት በእጅህም ሆነ በግንባርህ ላይ እንደ ምልክት ይሆናል።”

17 ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ አቋራጭ ቢሆንም እንኳ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በፍልስጥኤም ምድር በሚያልፈው መንገድ አልመራቸውም “ጦርነት ቢያጋጥማቸው ሐሳባቸውን ለውጠው ወደ ግብፅ ይመለሱ ይሆናል” ብሎአልና።

18 ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሕዝቡን ዙሪያ በሆነው በምድረ በዳው መንገድ ወደ ቀይ ባሕር መራቸው፤ እስራኤላውያንም ለጦርነት ዝግጁ ሆነው ከግብፅ ወጡ።

19 ዮሴፍ፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በእርግጥ ይጐበኛችኋል፤ በዚያን ጊዜም ዐፅሜን ይዛችሁ ከዚች ምድር መውጣት አለባችሁ ብሎ የእስራኤልን ልጆች አስምሎአቸው ስለ ነበር ሙሴ የዮሴፍን ዐፅም ይዞ ወጣ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሕዝቡን ዙሪያ በሆነው በምድረ በዳው መንገድ ወደ ቀይ ባህር መራቸው፤ እስራኤላውያንም ለጦርነት ዝግጁ ሆነው ከግብፅ ወጡ።

20 እነርሱም ከሱኮት ከተነሡ በኋላ ከምድረ በዳው ጥግ ባለው በኤታም ሰፈሩ።

21 ስለዚህ በቀንም ሆነ በሌሊት መጓዝ ይችሉ ዘንድ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በቀን በመንገዳቸው ሊመራቸው በደመና ዓምድ፣ በሌሊት ደግሞ ብርሃን ሊሰጣቸው በእሳት ዓምድ በፊታቸው ይሄድ ነበር።

22 በቀንም ሆነ በሌሊት የደመናውና የእሳቱ ዓምድ ከሕዝቡ ፊት የተለየበት ጊዜ አልነበረም።