ዘፀአት 15:19-25 NASV

19 የፈርዖን ፈረሶች፣ ሠረገሎቹና ፈረሰኞቹ ወደ ባሕሩ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) የባሕሩን ውሃ በላያቸው ላይ መለሰባቸው፤ እስራኤላውያን ግን በባሕሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ተሻገሩ።

20 ከዚያም የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያም ከበሮዋን አንሥታ ያዘች፤ የቀሩትም ሴቶች ሁሉ ከበሮ ይዘው እያሸበሸቡ ተከተሏት።

21 ማርያምም፣“ፈረሱንና ፈረሰኛውን፣በባሕር ውስጥ ጥሎአል፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዘምሩ፤እጅግ ከፍ ከፍ ብሎአልና”እያለች ዘመረችላቸው።

22 ከዚያም ሙሴ እስራኤልን ከቀይ ባሕር እየመራቸው ወደ ሱር ምድረ በዳ ሄዱ፤ ለሦስት ቀናት ውሃ ሳያገኙም በምድረ በዳ ተጓዙ።

23 ማራ በደረሱ ጊዜ ውሃው መራራ ስለ ነበር ሊጠጡት አልቻሉም፤ ቦታው ማራ ተብሎ የተጠራውም ከዚህ የተነሣ ነው።

24 ሕዝቡም በሙሴ ላይ በማጉረምረም፣ “ምን እንጠጣ?” አሉ።

25 ከዚያም ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኸ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) አንዲት ዛፍ አሳየው፤ ዕንጨቷንም ወደ ውሃው ጣላት፤ ውሃውም ጣፋጭ ሆነ።በዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሕግና ሥርዐት አበጀላቸው፤ በዚያም ሥፍራ ፈተናቸው።