ዘፀአት 15:21-27 NASV

21 ማርያምም፣“ፈረሱንና ፈረሰኛውን፣በባሕር ውስጥ ጥሎአል፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዘምሩ፤እጅግ ከፍ ከፍ ብሎአልና”እያለች ዘመረችላቸው።

22 ከዚያም ሙሴ እስራኤልን ከቀይ ባሕር እየመራቸው ወደ ሱር ምድረ በዳ ሄዱ፤ ለሦስት ቀናት ውሃ ሳያገኙም በምድረ በዳ ተጓዙ።

23 ማራ በደረሱ ጊዜ ውሃው መራራ ስለ ነበር ሊጠጡት አልቻሉም፤ ቦታው ማራ ተብሎ የተጠራውም ከዚህ የተነሣ ነው።

24 ሕዝቡም በሙሴ ላይ በማጉረምረም፣ “ምን እንጠጣ?” አሉ።

25 ከዚያም ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኸ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) አንዲት ዛፍ አሳየው፤ ዕንጨቷንም ወደ ውሃው ጣላት፤ ውሃውም ጣፋጭ ሆነ።በዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሕግና ሥርዐት አበጀላቸው፤ በዚያም ሥፍራ ፈተናቸው።

26 እርሱም አለ፤ “የአምላካችሁን እግዚአብሔር (ያህዌ) ድምፅ በጥንቃቄ ብትሰሙ፣ በፊቱም ትክክል የሆነውን ብትፈጽሙ፣ ትእዛዛቱን ልብ ብትሉና ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቁ፣ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁባቸውን ማንኛውንም ዐይነት በሽታ በእናንተ ላይ አላመጣም፤ ፈዋሻችሁ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝና።”

27 ከዚያም ዐሥራ ሁለት ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች ወዳሉበት ወደ ኤሊም መጡ፤ እነርሱም በውሃው አጠገብ በዚያ ሰፈሩ።