ዘፀአት 16:6-12 NASV

6 ስለዚህ ሙሴና አሮን ለእስራኤላውያን ሁሉ፣ እንዲህ አሉ፤ “ከግብፅ ምድር ያወጣችሁ እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኑን በዛሬይቱ ምሽት ታውቃላችሁ።

7 በእርሱ ላይ ያሰማችሁትን ማጒረምረም ሰምቷልና በማለዳ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ክብር ታያላችሁ፤ ለመሆኑ በእኛስ ላይ የምታጒረመርሙት እኛ ምንድን ነንና ነው?” አሏቸው።

8 ሙሴም ንግግሩን በመቀጠል፣ “በእርሱ ላይ ማጒረምረማችሁን ሰምቶአልና በምሽት የምትበሉትን ሥጋ፣ በማለዳም የምትፈልጉትን ያህል እንጀራ በሚሰጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኑን ታውቃላችሁ፤ እኛ ማን ነን? በእኛ ላይ አይደለም ያጒረመረማችሁት፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ ነው እንጂ” አላቸው።

9 ከዚያም ሙሴ አሮንን፣ “ ‘ማጒረምረማችሁን እርሱ ሰምቶአልና ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቅረቡ’ ብለህ ለመላው የእስራኤል ማኅበር ተናገር” አለው።

10 አሮንም ለመላው የእስራኤል ማኅበር ሲናገር ሳለ ወደ ምድረ በዳው ተመለከቱ፤ በዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ክብር በደመናው ላይ ተገልጦ ይታይ ነበር።

11 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

12 “የእስራኤላውያንን ማጒረምረም ሰምቻለሁ፤ ይህን ንገራቸው፤ ‘ፀሓይ ከመጥለቋ በፊት ሥጋ ትበላላችሁ፤ ሲነጋም እንጀራ ትበላላችሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) መሆኔን ታውቃላችሁ።’ ”