10 ስለዚህ ኢያሱ ሙሴ ባዘዘው መሠረት ከአማሌቃውያን ጋር ተዋጋ፤ ሙሴ፣ አሮንና ሖርም ወደ ኰረብታው ጫፍ ወጡ።
11 ሙሴ እጆቹን ወደ ላይ በሚያነሣበት ጊዜ ሁሉ እስራኤላውያን ድል ያደርጉ ነበር። እጆቹን ባወረደ ጊዜ ግን አማሌቃውያን ያሸንፉ ነበር።
12 የሙሴ እጆች እየዛሉ በሄዱ ጊዜ ድንጋይ ወስደው ከበታቹ አደረጉ፤ እርሱም ተቀመጠበት፤ አሮንና ሖርም አንዱ በአንዱ በኩል ሌላውም በሌላ በኩል ሆነው እጆቹን ወደ ላይ ያዙ። ይኸውም እጆቹ ፀሓይ እስክትጠልቅ ድረስ ጸንተው እንዲቆዩ ነው።
13 ስለዚህ ኢያሱ የአማሌቃውያንን ሰራዊት በሰይፍ ድል አደረገ።
14 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “ሲታወስ እንዲኖር ይህን በጥቅልል መጽሐፍ ላይ ጻፈው፤ ኢያሱም መስማቱን አረጋግጥ፤ ምክንያቱም የአማሌቃውያንን ዝክር ከሰማይ በታች ፈፅሜ እደመስሳለሁ” አለው።
15 ሙሴም መሠዊያውን ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) አርማዬ ነው” ብሎ ሰየመው።
16 “እጆች ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዙፋን ተዘርግተዋልና፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) አማሌቃውያንን ከትውልድ እስከ ትውልድ ይዋጋቸዋል” አለ።