10 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ሕዝቡ ሂድና ዛሬና ነገ ቀድሳቸው፤ ልብሳቸውን እንዲያጥቡ አድርግ፤
11 በሦስተኛውም ቀን ይዘጋጁ፤ ምክንያቱም በዚያ ቀን በሕዝቡ ፊት እግዚአብሔር (ያህዌ) በሲና ተራራ ላይ ይወርዳል።
12 በተራራው ዙሪያ ለሕዝቡ ወሰን አበጅተህ እንዲህ በላቸው፤ ‘ወደ ተራራው እንዳትወጡ ወይም ግርጌውን እንዳትነኩ ተጠንቀቁ፤ ማንም ተራራውን ቢነካ በርግጥ ይሞታል።
13 በድንጋይ ይወገራል ወይም በቀስት ይወጋል፤ ምንም እጅ በእርሱ ላይ አያርፍም፤ ሰውም ሆነ እንስሳ በሕይወት እንዲኖር አይተውም።’ ወደ ተራራው መውጣት የሚችሉት ከፍ ባለ ድምፅ መለከት በተነፋ ጊዜ ብቻ ነው።
14 ሙሴ ከተራራው ወርዶ ወደ ሕዝቡ ከሄደ በኋላ ቀደሳቸው፤ ልብሳቸውንም አጠቡ።
15 ከዚያም ለሕዝቡ፣ “ለሦስተኛው ቀን ራሳችሁን አዘጋጁ፤ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከማድረግ ተቈጠቡ” አላቸው።
16 በሦስተኛውም ቀን ጧት ከባድ ደመና በተራራው ላይ ሆኖ ነጎድጓድና መብረቅ እንዲሁም ታላቅ የቀንደ መለከት ድምፅ ነበር፤ በሰፈሩ ያሉት ሁሉ ተንቀጠቀጡ።