ዘፀአት 2:14-20 NASV

14 ሰውየውም፣ “አንተን በእኛ ላይ ገዥና ዳኛ ማን አደረገህ? ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋለህን?” አለው። ሙሴም፣ “ለካስ ያደረግሁት ነገር ታውቆአል!” በማለት ፈራ።

15 ፈርዖንም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ፤ ሙሴ ግን ከፈርዖን ሸሽቶ ወደ ምድያም ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሰ በአንድ የውሃ ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ።

16 የምድያም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ውሃው ጒድጓድ መጥተው የአባታቸውን በጎች ውሃ ለማጠጣት ገንዳውን ሞሉት።

17 እረኞችም መጥተው ሴቶቹን ሲያባርሯቸው ሙሴ ከተቀመጠበት ተነሥቶ ተከላከለላቸው፤ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው።

18 ሴቶቹም ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤል በተመለሱ ጊዜ፣ “ዛሬስ ያለወትሮአችሁ እንዴት ፈጥናችሁ ተመለሳችሁ?” አላቸው።

19 እነርሱም፣ “አንድ ግብፃዊ ከእረኞች እጅ አዳነን፤ እንዲያውም ውሃ ቀድቶ በጎቻችንን አጠጣልን” አሉት።

20 አባታቸውም፣ “ሴቶች ልጆቹን የት አለ? ለምን ትታችሁት መጣችሁ? ጥሩትና አብሮን እንጀራ ይብላ” አላቸው።