ዘፀአት 2:3-9 NASV

3 ከዚያ በላይ ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ ግን የደንገል ቅርጫት ወስዳ፣ በዝፍትና በቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም በውስጡ አስተኝታ ቅርጫቱን አባይ ወንዝ ዳር ቄጠማ መካከል አስቀመጠችው።

4 የሕፃኑም እኅት የሚደርስበትን ነገር ለማወቅ ራቅ ብላ ቆማ ታይ ነበር።

5 በዚህ ጊዜ የፈርዖን ልጅ ልትታጠብ ወደ አባይ ወንዝ ወረደች፤ በምትታጠብበትም ጊዜ ደንገጥሮቿ በወንዙ ዳር ወዲያና ወዲህ ይሉ ነበር፤ በቄጠማውም መካከል የተቀመጠ ቅርጫት አይታ ከደንገጥሮቿ አንዷን እንድ ታመጣው ላከቻት።

6 ቅርጫቱን ስትከፍተው ሕፃኑን በውስጡ አየች፤ ያለቅስ ስለ ነበርም አዘነችለትና፣ “ከዕብራውያን ሕፃናት አንዱ መሆን አለበት” አለች።

7 የሕፃኑ እኅት ለፈርዖን ልጅ፣ “ሕፃኑን እያጠባች የምታሳድግልሽ ከዕብራውያን ሴቶች መካከል ሞግዚት ላምጣልሽን?” አለቻት።

8 የፈርዖንም ልጅ፣ “መልካም፣ ሂጂ” አለቻት። ልጂቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ይዛ መጣች።

9 የፈርዖንም ልጅ ሴቲቱን፣ “ይህን ሕፃን ወስደሽ እያጠባሽ አሳድጊልኝ፤ ደመወዝ እከፍልሻለሁ” አለቻት። ሴትዮዋም ሕፃኑን ወስዳ አሳደገችው።