ዘፀአት 2:8-14 NASV

8 የፈርዖንም ልጅ፣ “መልካም፣ ሂጂ” አለቻት። ልጂቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ይዛ መጣች።

9 የፈርዖንም ልጅ ሴቲቱን፣ “ይህን ሕፃን ወስደሽ እያጠባሽ አሳድጊልኝ፤ ደመወዝ እከፍልሻለሁ” አለቻት። ሴትዮዋም ሕፃኑን ወስዳ አሳደገችው።

10 ሕፃኑም ባደገ ጊዜ ወደ ፈርዖን ልጅ አመጣችው ልጇም ሆነ፤ እርሷም፣ “ከውሃ አውጥቼዋለሁና” ስትል ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው።

11 ሙሴ ካደገ በኋላ አንድ ቀን ወገኖቹ ወደሚገኙበት ስፍራ ወጣ፤ በዚያም ተገድደው ከባድ ሥራ ሲሠሩ ተመለከተ፤ ዕብራዊ ወገኑንም አንድ ግብፃዊ ሲደበድበው አየ።

12 ሙሴም አካባቢውን ቃኝቶ ማንም አለመኖሩን ካረጋገጠ በኋላ፣ ግብፃዊውን ገድሎ አሸዋ ውስጥ ደበቀው።

13 በማግሥቱም በወጣ ጊዜ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አየ፤ ጥፋተኛውንም፣ “የገዛ ወገንህን የምትመታው ለምንድን ነው?” አለው።

14 ሰውየውም፣ “አንተን በእኛ ላይ ገዥና ዳኛ ማን አደረገህ? ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋለህን?” አለው። ሙሴም፣ “ለካስ ያደረግሁት ነገር ታውቆአል!” በማለት ፈራ።