ዘፀአት 22:1-7 NASV

1 “አንድ ሰው በሬ ወይም በግ ሰርቆ ቢያርድ ወይም ቢሸጥ በአንድ በሬ ምትክ አምስት በሬዎች፤ በአንድ በግ ምትክ አራት በጎች ይክፈል።

2 “አንድ ሌባ በር ሲሰብር ተይዞ ቢደበደብና ቢሞት፣ ተከላካዩ የደም ባለ ዕዳ አይሆንም፤

3 ነገር ግን ፀሓይ ከወጣች በኋላ ከተፈጸመ፣ ሰውየው በነፍስ ግድያ ይጠየቃል።“ሌባ የሰረቀውን መክፈል አለበት፤ ምንም ከሌለው ግን የሰረቀውን ይከፍል ዘንድ ይሸጥ።

4 “የሰረቀው እንስሳ በሬ ወይም አህያ፣ ወይም በግ ከነሕይወቱ በእጁ ከተያዘ እጥፍ መክፈል አለበት።

5 “አንድ ሰው ከብቶቹን በመስክ ወይም በወይን ቦታ አሰማርቶ እንዲሁ ስድ ቢለቃቸውና የሌላውን ሰው መስክ ቢግጡ፣ ምርጥ ከሆነው ከራሱ መስክ ወይም የወይን ቦታ መክፈል አለበት።

6 “እሳት ተነሥቶ ወደ ቍጥቋጦ ቢዘምትና ክምርን ወይም ያልታጨደን እህል ወይም አዝመራውን እንዳለ ቢበላ፣ እሳቱን ያቀጣጠለው ሰው ካሣ ይክፈል።

7 “አንድ ሰው ብሩ ወይም ንብረቱ ያለ ሥጋት ይጠበቅለት ዘንድ ለጎረቤቱ ሰጥቶ ሳለ ቢሰርቅበትና፣ ሌባው ቢያዝ እጥፍ ይክፈል፤