ዘፀአት 24:4-10 NASV

4 ከዚያም ሙሴ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለውን ሁሉ ጻፈ። በማግሥቱም ማልዶ ተነሥቶ፣ በተራራው ግርጌ መሠዊያን ሠራ፤ አሥራ ሁለቱን የእስራኤልን ነገዶች የሚወክሉ ዐሥራ ሁለት የድንጋይ ዐምዶችን አቆመ።

5 ከዚያም ወጣት ወንድ እስራኤላውያንን ላከ፤ እነርሱም የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ፤ ወይፈኖችን የኅብረት መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሠዉ።

6 ሙሴ የደሙን እኩሌታ ወስዶ በጎድጓዳ ሣህኖች አኖረው፤ የቀረውንም እኩሌታ በመሠዊያው ላይ ረጨው።

7 ከዚያም የኪዳኑን መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው፤ እነርሱም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለውን ሁሉ እናደርጋለን፤ እንታዘዛለን” አሉ።

8 ከዚያም ሙሴ ደሙን ወሰደ፤ ሕዝቡም ላይ ረጭቶ፣ “ይህ እነዚህን ቃሎች በሰጠ ጊዜ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእናንተ ጋር የገባው የቃል ኪዳኑ ደም ነው” አላቸው።

9 ሙሴና አሮን፣ ናዳብና አብድዩ እንደዚሁም ሰባዎቹ የእስራኤል አለቆች ወደ ተራራው ወጡ፣

10 የእስራኤልንም አምላክ (ኤሎሂም) አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ብሩህ ሰማይ የጠራ የሰንፔር ወለል ነበር።