21 የስርየት መክደኛውን በታቦቱ አናት ላይ አስቀምጠው፤ እኔ የምሰጥህን ምስክሩንም በታቦቱ ውስጥ አስቀምጥ።
22 በምስክሩ ታቦት ላይ ባሉት በሁለቱ ኪሩቤል መካከል፣ በስርየት መክደኛው ላይ በዚያ እኔ ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ ለእስራኤላውያን የሚሆኑትን ትእዛዞቼንም እሰጥሃለሁ።
23 ርዝመቱ ሁለት ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ፣ ከፍታው አንድ ክንድ ተኩልጨ የሆነ ጠረጴዛ ከግራር ዕንጨት ሥራ።
24 በንጹሕ ወርቅ ለብጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አድርግለት።
25 ዙሪያውንም አንድ ስንዝር ስፋት ያለው ጠርዝ አብጅለት፤ በጠርዙም ዙሪያ የወርቅ ክፈፍ አድርግለት።
26 ለጠረጴዛው አራት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተህ፣ አራቱ እግሮች ባሉበት በአራቱ ማእዘኖች ላይ አያይዘው።
27 ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች ይይዙ ዘንድ፣ ቀለበቶቹ ከክፈፉ አጠገብ ይሁኑ።