26 “ደግሞም ከግራር ዕንጨት አግዳሚዎችን አብጅ፤ በአንድ በኩል ላሉት የማደሪያው ድንኳን ወጋግራዎች አምስት፣
27 በሌላው ጎን ላሉት አምስት፣ በማደሪያው ድንኳን ዳር በምዕራብ በኩል ባሉት ወጋግራዎች አምስት አብጅ።
28 መካከለኛው አግዳሚ በወጋግራዎቹ መካከል ከጫፍ እስከ ጫፍ ይተላለፍ።
29 ወጋግራዎቹን በወርቅ ለብጣቸው፤ አግዳሚዎቹን ለመያዝ የወርቅ ቀለበቶች አብጅ፤ አግዳሚዎቹንም በወርቅ ለብጣቸው።
30 “ማደሪያ ድንኳኑንም በተራራው ላይ ባየኸው ዕቅድ መሠረት ትከለው።
31 “ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ መጋረጃ አብጅ፤ እጀ ብልህ ሠራተኛም ኪሩቤልን ይጥለፍበት።
32 በወርቅ በተለበጡ ከግራር ዕንጨት በተሠሩና በአራቱ የብር መቆሚያዎች ላይ በቆሙት በአራቱ ምሰሶዎች፣ በወርቅ ኵላቦች ላይ አንጠልጥለው።