30 “ማደሪያ ድንኳኑንም በተራራው ላይ ባየኸው ዕቅድ መሠረት ትከለው።
31 “ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ መጋረጃ አብጅ፤ እጀ ብልህ ሠራተኛም ኪሩቤልን ይጥለፍበት።
32 በወርቅ በተለበጡ ከግራር ዕንጨት በተሠሩና በአራቱ የብር መቆሚያዎች ላይ በቆሙት በአራቱ ምሰሶዎች፣ በወርቅ ኵላቦች ላይ አንጠልጥለው።
33 መጋረጃውን በማያያዣዎቹ ላይ ስቀለው፤ የምስክሩንም ታቦት ከመጋረጃው በስተ ኋላ አስቀምጠው፤ መጋረጃውም መቅደሱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ ይለያል።
34 በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ በምስክሩ ታቦት ላይ የማስተስረያውን ክዳን አስቀምጥ።
35 ጠረጴዛውን ከመገናኛው ድንኳን በሰሜን በኩል ከመጋረጃው ውስጥ አስቀምጠው፤ መቅረዙንም ከእርሱ ትይዩ በማድረግ በደቡብ በኩል አድርገው።
36 “ለድንኳኑ ደጃፍ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ በጥልፍ ዐዋቂ የተጠለፈ መጋረጃ አብጅ።