6 የግራር ዕንጨት መሎጊያዎችን ለመሠዊያው ሠርተህ በነሐስ ለብጣቸው።
7 በሸክም ጊዜ በመሠዊያው ሁለቱም ጎኖች እንዲሆኑ፣ መሎጊያዎቹ በቀለበቶቹ ውስጥ ይግቡ።
8 መሠዊያውን ውስጡን ባዶ ከሆኑ ሳንቃዎች አብጀው፤ ልክ በተራራው ላይ ባየኸው መሠረት ይበጅ።
9 “ለመገናኛው ድንኳን አደባባይ አብጅለት፤ በደቡብ በኩል ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ ይሁን፣ ከቀጭን በፍታ የተፈተሉ መጋረጃዎች፣
10 ሃያ ምሰሶዎች፣ ሃያ የነሐስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹም ላይ ዘንጎች ይኑሩት።
11 በሰሜኑም በኩል አንድ መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ይሁኑ፤ ሃያ ምሰሶዎቹ፣ ሃያ የነሐስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎችም ላይ ዘንጎች ይኑሩ።
12 “የአደባባዩ ምዕራብ ጫፍ ስፋቱ አምሳ ክንድ ሆኖ ዐሥር ምሰሶዎችና ዐሥር መቆሚያዎች ያሉት መጋረጃዎች ይኑሩት።