1 “ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ ከእስራኤላውያን መካከል ወንድምህ አሮንን ከወንዶች ልጆቹ ከናዳብ፣ ከአብ ዩድ፣ ከአልዓዛርና ከኢታምር ጋር ወደ አንተ አቅርባቸው።
2 ለእርሱም ማዕረግና ክብር ለመስጠት ለወንድምህ ለአሮን የተቀደሱ መጐናጸፊያዎችን አብጅለት።
3 ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ የተለየ ይሆን ዘንድ ጥበብ ለሰጠኋቸው በዚህ ጒዳይ ላይ ጥበበኛ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ለአሮን መጐናጸፊያዎችን እንዲሠሩለት ንገራቸው።
4 የሚሠሯቸው መጐናጸፊያዎች የደረት ልብስ ኤፉድ ቀሚስ፣ ጥልፍ ሸሚዝ፣ ጥምጥምና መታጠቂያ ናቸው፤ ካህን ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ የተቀደሱ መጐናጸፊያዎችን ለአሮንና ለወንድ ልጆቹ ይሠራሉ።
5 ወርቅ፣ ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና እንዲሁም ቀጭን በፍታ ይጠቀሙ።