10 እንደ ልደታቸው ቅደም ተከተል ስድስቱን ስሞች በአንዱ ድንጋይ ላይ የቀሩትንም ስሞች በሌላው ላይ ቅረጽባቸው።
11 የቅርጽ ሠራተኛ ማኅተም እንደሚቀርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም በሁለቱ ድንጋዮች ላይ ቅረጽ፤ ከዚያም ድንጋዮቹን በወርቅ ፈርጥ ክፈፋቸው፤
12 ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ በኤፉዱ ትከሻ ላይ ካሉት ንጣዮች ጋር አያይዛቸው፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት መታሰቢያ እንዲሆኑ አሮን ስሞቹን በትከሻው ላይ ይሸከማቸው።
13 የወርቅ ፈርጦችን አብጅ፣
14 እንደ ገመድ ያሉ ሁለት በንጹሕ ወርቅ የተጐነጐኑ ድሪዎችን አብጅተህ ከፈርጡ ጋር አያይዛቸው።
15 “የፍርድ መስጫውን የደረት ኪስ ብልኅ ሠራተኛ እንደሚሠራው አድርገህ አብጀው፤ ልክ እንደ ኤፉዱ ከወርቅ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ አብጀው።
16 ርዝመቱ አንድ ስንዝር፣ ስፋቱ አንድ ስንዝር ሆኖ ባለ አራት ማእዘንና በድርቡ የታጠፈ ይሁን።