33 ለክህነታቸውና ለመቀደሳቸው ማስተስረያ የሆኑትን እነዚህን መሥዋዕቶችን ይብሉ፤ የተቀደሱ ስለሆኑ ሌላ ማንም አይብላቸው።
34 ከክህነቱ የአውራ በግ ሥጋ ወይም ከቂጣው እስከ ንጋት ድረስ ቢተርፍ አቃጥለው፤ የተቀደሰ ስለ ሆነ መበላት የለበትም።
35 “ክህነታቸውን በሰባት ቀን በመፈጸም ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ያዘዝሁህን ሁሉ አድርግላቸው።
36 ለማስተስረያ የሚሆን አንድ ወይፈን የኀጢአት መሥዋዕት አድርገህ በየዕለቱ ሠዋ፤ ለመሠዊያውም ማስተስረያ በማቅረብ መሠዊያውን አንጻው፤ ትቀድሰውም ዘንድ ቅባው።
37 ለሰባት ቀን ለመሠዊያው ማስተስረያ በማድረግ ቀድሰው፤ ከዚያም መሠዊያው እጅግ የተቀደሰ ይሆናል፤ የሚነካውም ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል።
38 “በየዕለቱ ያለ ማቋረጥ በመሠዊያው ላይ የምታቀርበው ይህ ነው፤ ዓመት የሞላቸው ሁለት የበግ ጠቦቶች፤
39 አንዱን በማለዳ፣ ሌላውን በምሽት አቅርብ።