9 የራስ ማሰሪያዎችንም አድርግላቸው፤ ከዚያም አሮንንና ወንዶች ልጆቹን መታጠቂያዎችን አስታጥቃቸው፤ ክህነት የዘላለም ሥርዐት ይሆንላቸዋል፤ በዚህም መንገድ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ትክናቸዋለህ።
10 “ወይፈኑን በመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት በማምጣት አሮንና ወንዶች ልጆቹ በራሱ ላይ እጆቻቸውን ይጫኑበት።
11 በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እረደው።
12 ከወይፈኑ ደም ወስደህ በመሠዊያው ቀንዶች ላይ በጣቶችህ አድርግበት፤ የቀረውንም ከመሠዊያው ሥር አፍሰው።
13 ከዚያም በሆድ ዕቃዎች ያለውን ስብ ሁሉ፣ የጉበቱን መሸፈኛና ሁለቱንም ኵላሊቶች በዙሪያቸው ካለው ስብ ጋር ወስደህ በመሠዊያው ላይ አቃጥላቸው።
14 ነገር ግን የወይፈኑን ሥጋ፣ ቆዳውንና የማይበላውን አሰስ ገሠስ ሥጋ ከሰፈር ውጭ አቃጥለው፤ የኀጢአት መሥዋዕት ነው።
15 “ከሁለቱ አውራ በጎች አንዱን ወስደህ፣ አሮንና ወንዶች ልጆቹ በራሱ ላይ እጃቸውን ይጭኑበታል።