ዘፀአት 3:5-11 NASV

5 እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “ወደዚህ እንዳትቀርብ፤ ይህች የቆምኽባት ምድር የተቀደሰች ስለሆነች ጫማህን አውልቅ” አለው

6 ቀጥሎም፣ “እኔ የአባቶችህ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ (ኤሎሂም) ነኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ሙሴ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ።

7 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ እንዲህ አለ “በግብፅ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ።

8 ስለዚህም ከግብፃውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈሰው ሰፊና ለም ወደሆነችው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ።

9 አሁንም የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ደርሷል፤ ግብፃውያን የሚያደርሱባቸውን ግፍ አይቻለሁ።

10 በል እንግዲህ ና፤ ሕዝቤን፣ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር እንድታወጣቸው ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ”።

11 ሙሴ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም)፣ “ወደ ፈርዖን የምሄድና የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ? አለው።