8 ምሽት ላይ መብራቶቹን በሚያበራበትም ጊዜ ዕጣኑን ማጠን አለበት፤ ይኸውም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ዕጣኑ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ዘወትር እንዲጤስ ነው።
9 በዚህም መሠዊያ ላይ ሌላ ዕጣን ወይም ሌላ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የእህል መሥዋዕት አታቅርብ፤ የመጠጥ መሥዋዕትም አታፍስበት።
10 አሮን በዓመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተስረያ ያደርግበታል፤ ይህ ዓመታዊ ማስተስረያ በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ለማስተስረያ ከሚሆን የኀጢአት መስዋዕት ደም ጋር መደረግ አለበት፤ ይህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) እጅግ ቅዱስ ነው።”
11 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤
12 “የእስራኤላውያንን ጠቅላላ ቈጠራ በምታደርግበት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው በሚቈጠርበት ወቅት ለሕይወቱ ቤዛ የሚሆን ወጆ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መክፈል አለበት፤ በዚህም ዐይነት ስትቈጥራቸው በእነርሱ ላይ መቅሠፍት አይመጣም።
13 ማንም ወደ ተቈጠሩት ዘንድ የሚያልፍ ሃያ አቦሊ በሚመዝን በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግማሽ ሰቅል መስጠት አለበት፤ ይህ ግማሽ ሰቅል ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።
14 ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከሃያ በላይ ሆኖ ወደ ተቈጠሩት ያለፉት ሁሉ፣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት ማቅረብ አለባቸው።